..... አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስለ እመቤታችን
በመጽሐፈ አርጋኖን ከጻፉት .....
† የሰማይ ሥርዓት በምድር ላይ ተሠራ፡፡
† እመቤታችን የተመረጠች ድንግል የሰማዩን ሠራዊት አሰገደቻቸው፡፡ የዓለም ጌጥ ሽልማት የሁሉ አባት የሚሆን መላእክትን የፈጠረ ጌታ ከእርሷ ተወልዷልና፡፡
† ድንግል ሆይ ክብርሽን ገናንነትሽን ለመናገር የሚቻለው ማነው? ምስጋናሽን ለመናገር ማን ይችላል? ከፍጡራንም ወገን ሁሉ አንቺን የሚመስል የለም፡፡
† መላእክት የመላእክት አለቆች ያመሰግኑሻል፡፡ የፈጠራቸውን ወልደሽዋልና፡፡
† ሰውና እንስሳ ሥጋም የለበሰ ፍጥረት ሁሉ ያደንቁሻል፡፡ ያመሰግኑሻል፡፡ በዝናብ አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ የሚመግባቸው እርሱን በድንግልናሽ ወተት አሳድገሽዋልና፡፡
† ኪሩቤል ሱራፌል ይሰግዱልሻል፡፡ በላያቸው የሚቀመጥ እርሱን በጀርባሽ አዝለሽዋልና፡፡
† አንድ ልጅሽ ወደ ሰማይ ባረገና በባሕርይ አባቱ በስተቀኝ በተቀመጠ ጊዜ ካንቺ የነሣው ትስብእት ከመለኮት ጋራ አንድ ሆኖ ከዚያ አለ፡፡
† ድንግል ሆይ ባማረው በተወደደው ነገር ሁሉ መሰልሁሽ ምስጋናሽን ግን ለመፈጸም አልቻልኩም፡፡
† ማኅበረ መላእክት ሁሉ ያመሰግንሻል፤ በንጽሕና ስርዓት እነርሱን መስለሻልና፡፡
† ማኅበረ ነቢያት ሁላቸው ያመሰግኑሻል፤ ትንቢታቸው ባንቺ ተፈጽሟልና፡፡
† የሐዋርያት ማኅበር ያመሰግኑሻል፤ የተወደደ ልጅሽ ወንድም ሆኗቸዋልና፡፡ ለመንግስቱም ወራሾች አድርጓቸዋልና፡፡
† የበጎ ጎልማሶች ሰማዕታት ያመሰግኑሻል፤ የልጅሽ መከራ አንድነት በስጋቸው ተቀብለዋልና፡፡
† ደናግል መነኮሳት ያመሰግኑሻል፤ አኗኗራቸውን ለንጽሕናሽ አምሳል ብፅዓት አድርገዋልና፡፡
† ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስቆጶሳት ያመሰግኑሻል፤ የልጅሽ አንደበት ስልጣን በአንደበታቸው ተዋህዷልና፡፡
† ከፍጥረት ወገኖች ሁሉ ካንቺ የሚከብር እንደሌለ እንግዲህ አወቅሁ፡፡
† ካንቺ የተወለደው እግዚአብሔር እንደሆነ የማያምን፤ እርሱንም ከወለድሽ በኋላ በድንግልና እንደኖርሽ የማያምን ርጉም ነው፡፡
† ድንግል ሆይ የሚወዱሽ የተወደዱ ናቸው፡፡ ንግስት ሆይ የሚያከብሩሽ የከበሩ ናቸው፡፡ ንጽሕት ሆይ የሚቀድሱሽ ሁሉ የተቀደሱ ናቸው፡፡ ፍሥሕት ሆይ የሚመርቁሽ የተመረቁ ናቸው፡፡
† ልዕልት ሆይ የሚያደንቁሽ የተደነቁ ናቸው፡፡ ውድስት ሆይ ለንግሥትነትሽ የሚገዙ ሁሉ የተባረኩ ናቸው፡፡
† ሰይጣን ከቶ እንደ ጸሎት ማስታጎል የሚወደው የለም፡፡ ጸሎት ፍላጻ ነውና ዓይኑን ይወጋዋል፡፡ ከሚጸልይ ሰው አንደበት እሳት ወጥቶ ሰይጣንን ያቃጥለዋልና፡፡ ሰይጣንም ስለዚህ ከበጎ ሥራ ሁሉ ጸሎትና ትጋትን ይጠላል፡፡
† ይልቁንም ያንቺን ምስጋና ወሬ ሲሰማ በብስጭት ጥርሱን ያፋጫል፤ የምስጋናሽ ወሬ በእርሱ ዘንድ መራጃ ነውና ራሱን ይቆርጠዋል፡፡
† ከስምሽ አጠራር የተነሣ መብረቅ በኃይል ሲጮህ እንደሰማ ሁሉ ይደነግጣል፡፡ አንቺ ከተወለድሽ ጀምሮ ፈጽሞ ዕረፍት አላገኘም፡፡
† በአንቺ ታመመ በልጅሽ ተጨነቀ በአንድ ልጅሽ መስቀል ሥቃይ አገኘው፡፡ ከፍጡራን ወገኖች ሁሉ ይልቅ ሰይጣን አንቺን ይጠላል፡፡
† በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ የተመረጥሽ ድንግል እመቤቴ ማርያም ሆይ በሁሉ ተመሰልሽ በሁሉም መሰሉሽ አንቺን ግን የሚመስልሽ የለም፡፡
† ሰማይ አይተካከልሽም ምድርም የሆድሽን ስፋት ያህል አትሆንም፣ የማትችለውን ችለሽዋልና፡፡ የማትሸከመውንም ተሸከምሽ፡፡
† ኪሩቤል የልጅሽ ሠረገሎች ናቸው፡፡ ሱራፌልም ከበኩር ልጅሽ በታች ወድቀው ይገዛሉ፡፡ ክብር ለከፍታሽ ነው፣ ገናንነትም ለጌትነትሽ፡፡
† የአምላክም ይቅርታ በሰው ልጆች ላይ በአንቺ ጸና፡፡ የፍጡር ባሕርይ ከፈጣሪ ጋራ በአንቺ አንድ አካል አንድ ባሕርይ አንድ ገዥ ሆነ፡፡ ይህ ስራ እጅግ ድንቅ ነው፡፡
† ፈጣሪ ፍጡሩን መልበስ ይህ ትህትና እጅግ የተደነቀ ነው፡፡
† የውዳሴሽ ወሬ በዓለም ሁሉ ተሰምቷልና በመንፈስ ቅዱስ እንደተናገርሽ እንዲህ ስትይ ‹‹እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል፡፡›› ሉቃ.1፡48
† በእውነት ምስጋና ይገባሻል፤ የእግዚአብሔር እናቱ ሁነሻልና፡፡ በእውነት መደነቅ ይገባሻል፤ ዓለምን ሁሉ በመሐል እጁ የያዘ እርሱን ወልደሻልና፡፡ በእውነት ብፅዓን ይገባሻል፤ ለእውነተኛ ፀሐይ መውጫ ሆነሻልና፡፡
† በእውነት መመስገን ይገባሻል፤ ለማለዳው ኮከብ ምሥራቅ ሆነሻልና፡፡ በእውነት መደነቅ ይገባሻል፤ ለጥምቀት ልጆች መመኪያ ሆነሻልና፡፡ በእውነት ብፅዕና ይገባሻል፤ ለሃይማኖት መሠረት ጽናት ሆነሻልና፡፡
† ከኪሩቤል ክብር ገናንነት ለአንቺ ይገባል፡፡ ከሱራፌልም ውዳሴ ከመላእክትም እልልታ ከመላእክት አለቆችም ዝማሬ ለአንቺ ይገባል፡፡
† አምላክን የወለድሽ ቅድስት ድንግል ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ልጅ የወለድሽ ንዕድ ክብርት ሆይ፣ እውነተኛ ፀሐይን ያስገኘሽ የተመረጥሽ ድንግል ሆይ፣ ምን ብዬ እጠራሻለሁ? በምንስ ምሳሌ እመስልሻለሁ?
† የመለኮት ምንጣፍ የተነጠፈባት ንጽሕት አዳራሽ ሆይ፣ የንጽሕና ሙሽራ ቤት፣ ርኩሰት የሌለባት የመንፈስ ቅዱስ ሠርግ ቤት፡፡
† ከዕሴይ ሥር የተገኘች የወይን ሐረግ፣ ከዳዊት ግንድ የበቀለች በትር፤ ከእርሷም አበባ የወጣ ይኸውም የቅዱሳን መዓዛ ኢየሱስ ክርስቶስ (ኢሳ.11፡1)
† ለአዳምና ለልጆቹ ቤዛ የሚሆነውን የሕይወት መድኃኒት መሥዋዕት የምትሸከም መሠዊያ፡፡
† አንቺ ከወደድሽኝ ልጅሽ አይጠላኝም፡፡
† ልጅሽም ከወደደኝ በኃይልም ቢሆን በሹመትም፣ በተንኮልም፣ በምላስም፣ በሥራዬም፣ በዘመናይነትም ቢሆን የሚችለኝ የሚቃወመኝ የለም፡፡
† ነቢዩ ኢሳያስ እንደተናገረ እንዲህ ሲል፡- ‹‹እግዚአብሔር አምላካችን ከእኛ ጋራ ከሆነ የሚችለን የለም፡፡››
† ሳይዘሯት የምታፈራ ንጽሕት እርሻ እርሷም ለቁርባን ያማረ የተወደደ ስንዴ የተሰጠ ሳያጠጧት የለመለመች የወይን ሐረግ ለበዓልም መጠጥ ሊሆን የበረከት ፍሬ ከእርሷ የተገኘ፡፡
† ድንግል ግን በሥርዓት ከሴቶች ጋራ አልተባበረችም፡፡ መፅነሷ ልዩ ሆነ፣ መውለዷም ደግሞ ልዩ ነው፡፡
† የአሮን በትር በድንግል ተመሰለች፤ ሳይተክሏት ለምልማ፣ ውሃ ሳያጠጧት አብባ ተገኝታለችና (ዘኁ.17፡8)
† ቁልፏ ሳይከፈት ከውስጧ የሕይወት ውሃ የተቀዳባት የተቆለፈች የክብር አዘቅት፡፡
† ደጅዋ ሳይከፈት ፍሬዋ የተለቀመ የተዘጋች የተክል ቦታ ገልጾ ሊያነባት የሚችል የሌለ የታተመች መጽሐፍ በአለቆች ላይ አለቃ ለሚሆን በነገሥታትም ላይ ለሚነግሥ መቀመጫ የምትሆኚ ኪሩባዊት ሠረገላ፡፡
† የመለኮት አትሮኑስ የእሳትነቱን ነበልባል የተሸከመች ሥጋዊት ዙፋን የሰማይ ሁለተኛ ሰማይ
† ዝናማት ያላበቀሉትን፣ አየራት ያላሳደጉትን የሰማዩን እንጀራ ያስገኘች ቤተልሔማዊት መሶብ ሆይ፤
† የእሳቱን ነበልባል የተሸከመች ዕፀ ጳጦስ ሆይ እንጨቱ ሳይቃጠል እሳቱ ሳይጠፋ፡፡ (ዘጸ.3፡2 ፣ 16፡22)
† የመድኃኒት ብልቃጥ ድንግል ሆይ፣ ጸሎቴ በልጅሽ ፊት የተወደደ ይሁን፤ የሙሴ መሥዋዕት በምድረ በዳ፣ የአሮን መሥዋዕት በምስክሩ ድንኳን የተወደደ እንደሆነ፡፡
† በንጽሕናሽ መዓዛም የኃጢአቴን ክፉ ሽታ አርቂልኝ፡፡
† በወርቅ ዘርፍ ልብስ የተጎናጸፈች የተሸለመች ንግሥት ሆይ በየጊዜው በየሰዓቱ የንጽሕና ልብስ የቅድስናም መጎናጸፊያ እንድለብስ አድርጊኝ፡፡ (መዝ.45፡14)
† ድንግል ሆይ፣ የንጉሥ እናት ንግሥት እመቤቴ፣ የእግዚአብሔር እናት ክብርት የአምላክ እናት፣ ንጽሕት የንጹሕ ባሕርይ እናት፣ ሰማይ የፀሐይ መገኛ ቤተ መንግሥት፣ የመሢሕ እናት፣ ታቦት የሕግ እናት፡፡
† የኃጢአቴ ብዛት ከቁጥር ከስፍር የተረፈ ሆኗልና በልመናሽ አቅልይልኝ፡፡
† ………
† ድንግል ሳላቋርጥ አመሰግንሽ ዘንድ የኪሩቤልን አፍ፣ የሱራፌልን ልሳን ብቀበል፣ በዚህም ምስጋናሽን ለመፈጸም አልችልም፡፡ ልዑሉንም ምሥጢር እናገር ዘንድ እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል፣ የተሠወረውን ምሥጢርም እንደ ዮሐንስ የዕውቀት መጻሕፍትንም ብበላ በዚህም ውዳሴሽን ለመፈጸም አልችልም፡፡
† ድንግል ሆይ፣ ሰውነቴ ሁሉ አንደበት የተመላ ቢሆን፣ በአጥንቶቼም ቁጥር ዕውቀት ቢሰጠኝ፣ የራሴ ፀጉርም ሁሉ መናገር ቢሰጠው በዚህም ውዳሴሽን ለመፈፀም አልችልም፡፡
† ሰማይ በስፋቱ ብራና ቢሆን ባሕርም ቀለም ቢሆን ምስጋና የተመላውን ክብርሽን ገናንነትሽን ለመጻፍ በዚህም ምስጋናሽን ለመፈጸም አልችልም፡፡
† ………
† በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ የተመረጥሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ አካላዊ ቃልን የወለድሽው እሳትንም በሥጋ የወሰንሽ ድንግል እኔን ኃጢአተኛውን አማልጅኝ፡፡ ሥጋችንን እንደሰም ከሚያቀልጠው ከሥጋዊ ፈቃድ እሳትነት አድኝኝ፡፡
† ……….
† መጽሐፈ አርጋኖን በአብዛኛው ስለ ጌታ እናት ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ይናገራል፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጻፈው በጥቂቱ ብቻ ነው፡፡
† ድንግል ሆይ! በዳግም ምጽዓት በልጅሽ ቀኝ እንቆም ዘንድ ከልጅሽ ከፈጣሪሽ ለምኝልን!

አስተያየቶች