ነገረ ቅዱሳን 
(በውኑ ስለ ቅዱሳን መናገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለምን? ቤተክርስቲያን ለምን ስለ ቅዱሳን ታስተምራለች?)
- አንዳንድ አብዳን(ሰነፎች) 'ስለ ኢየሱስ ብቻ እንጂ ስለ ሌላ መናገር አያስፈልግም' ሲሉ ይደመጣሉ፤ 'ስለ ቅዱሳን መናገር ክርስቶስን ይሸፍነዋል' የሚሉም አሉ። በእውነት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "እኔን ብቻ አንጂ ስለኔ የተጋደሉ ቅዱሳንን አታንሱብኝ" ብሏልን? አባቶቻችን ሐዋርያትስ ወንጌልን ዞረው ስያስተምሩ በእምነትና በምግባር እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኙ ቅዱሳን አልተናገሩምን? 
 መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ ጌታችን 'እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም' በሚል ርዕስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ቅድስናና ክብር አስተምሯል(ማቴ 11:7-11፣ ዮሐ 5:35)። 'አንተ ብጹዕ ነህ' ብሎ ጴጥሮስንም አመስግኖታል(ማቴ 16:17)፤ ስለ ሐዋርያው ናትናኤልም 'ተንኮል የሌለበት የእሥራኤል ሰው' ብሎ ተናግሯል(ዮሐ 1:48)። ሐዋርያትን 'እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ያገኛል፤ እናንተን የጣለ እኔን ይጥላል፤ በአስራ ሁለቱ የእስራኤል ዙፋን ተቀምጣችሁ ትፈርዳላችሁ' ያለውም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው(ማቴ 10:40-41፣ ሉቃ 10:16፣ ማቴ 19:28)። 'እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ።'በማለት እነርሱ አካላቱ እንደኾኑም ተናግሯል(ዮሐ 15:5)። በእግሮቹ ላይ ሽቶን ስላፈሰሰች ሴትም 'እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።' ያለው እርሱ ነው(ማቴ 26:13)። ቅዱስ ጳውሎስንም 'የተመረጠ ዕቃ' ብለው ያወደሰውም እርሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው(ሐዋ 9:15)።
 ቅዱሳን ሐዋርያት፦ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በእምነት እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኙት ቅዱሳን ዜና ገድል 'እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል' ይለናል፤ ጊዜ ቢያጥርበትም አስፍቶ የቅዱሳንን ተጋድሎ ያወሳል(ዕብ 11:32-39)። ዳግመኛም ይኽ ሐዋርያ 'የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው' በማለት የቅዱሳንን ሕይወት መመልከት እንደሚገባ አስተምሯል(ዕብ 13:7)፤ የእነርሱን ሕይወት ለመመልከት ደግሞ ስለነሱ መማር ያስፈልጋል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም 'ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው።' የሚል ሰማያዊ ድምጽ እንደሰማ ጽፎልናል (ራእ14:13)።
 ስለ ቅዱሳን ተጋድሎና ክብር የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እጅግ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ፦ የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት ከምዕ.12 እስከ ምዕ. 18 እንዲሁም ከምዕ. 20 - 35 ድረስ ስለ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ሕይወት ሲናገር ከምዕ. 39 እስከ ምዕ. 50 ደግሞ ስለ ዮሴፍ ይናገራል። መጽሐፈ ኢዮብም ሙሉ ስለ ጻድቁ ኢዮብ ገድል ይናገራል። የሐዋርያት ሥራም የቅዱሳን ሐዋርያት አገልግሎትና ተጋድሎ በስፋት ያትታል።
 ቅድስት ቤተክርስቲያን ስለ ቅዱሳን የምታስተምርበት ዋንኛ ምክኒያት ምእመናን የቅዱሳንን ሕይወት በመመልከት ከእነርሱ ይማሩ ዘንድ ነው(ኢሳ 51:2፣ ሮሜ 16:18፣ 1ቆሮ 11:1፣ ዕብ 13:7)። አንድም የእግዚአብሔር ሥራው የሚገለጠው በእነርሱ ነውና(መዝ 15:2፣ መዝ 75(76):1)።
 ማጠቃለያ 
- ስለዚህም በእውነት ስለ ቅዱሳን መናገር መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ ነው። ስለ ቅዱሳን ስንናገር እግዚአብሔር እንዴት ለአገልግሎት እንደመረጣቸው፤ ክርስቶስን እንዴት እንዳገለገሉት፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዴት ተአምራትን እንዳደረጉ፤ ስለ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመሰክሩ ምን አይነት መከራ እንደገጠማቸው እንዲሁም በአካለ ሥጋ ሲያርፉ እግዚአብሔር እንዴት እንዳከበራቸው እንናገራለን። በዚህም ሁሉ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ከእነርሱ እንማራለን። 'ስለ ቅዱሳን መናገር ክርስቶስን ይሸፍናል' የሚሉም ሰዎች ዐላዋቂ መሆናቸውን በዚህ እንረዳለን።

አስተያየቶች