+++ ሙሴ ሆይ ተሸፈንልን! ++



ነቢዩ ሙሴ በብሉይ ኪዳን ለአርባ ቀንና ሌሊት ከጾሙ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ‹አርባ ቀን ሙሉ እህል በአፉ ሳይገባ እንዴት አልራበውም? እንዴትስ አስቻለው› የሚል ሰው ካለ ሙሴ ምን ሲያደርግ እንደሰነበተ ያላወቀ ሰው ነው፡፡ እነዚያን አርባ ቀናት ያሳለፈው በታላቁ የሲና ተራራ ላይ ነበር፡፡ በዚህ ቅዱስ ተራራ ራስ ላይ እንዲቆም የተነገረው ይህ ነቢይ በተራራው ጫፍ ላይ እንደደረሰ ድንገት ተራራው በደመና ተሸፈነ፡፡ ልዑል እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት!›› የሚል ታላቅ ግርማ ያለው ድምጽም በተራራው ላይ ተሰማ፡፡

ሙሴ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ በእግዚአብሔር ፊት ወድቆ ሰገደ፡፡ በአምላካዊ ብርሃን ውስጥ ተከብቦ ፣ በእሳት መጋረጃዎች ውስጥ እያለፈ ፣ የሠራዊት ጌታ የልዑል እግዚአብሔርን ድምጽ እየሰማ ለአርባ መዓልትና ሌሊቶች ከፈጣሪው ጋር ሲነጋገር ቆየ፡፡ ልብ በሉ! በእንዲህ ዓይነት መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ተውጦ የከረመ ሰው መቼ ፋታ አግኝቶ ሊርበውና ሊጠማው ይችላል? በመጠየቃችንም ራሳችንን ሳንታዘበው አንቀርም!

ከአርባ ቀናት በኋላ ሙሴ ከተራራው ሲወርድ በግራና በቀኝ ሁለቱን ጽላት ይዞ ነበር፡፡ ወደ ሕዝቡ ሲመጣ ግን ሕዝቡ ወደ ሙሴ እንዳይቀርቡ ያስፈራቸው አንድ ነገር ተፈጠረ፡፡ ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ ፊቱ ያበራ ነበር፡፡ በቅዱሱ ተራራ በደመናት መካከል ቆሞ ከፈጣሪው ጋር ቃል በቃል የተነጋገረው ይህ ታላቅ ሰው አርባ ቀንና ሌሊት ሳይመገብ ቢቆይም በረሃብ ከመጠውለግ ይልቅ ከአምላካዊ ጸጋ የተነሣ የፊቱ ብርሃን አንጸባረቀ፡፡ ይህንን ተአምር ያዩት እስራኤልም በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፡፡ ሙሴ ግን ‹ፊቱ እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር።›

የእግዚአብሔር ሰው ክብሩን ሌሎች ያዩለታል እንጂ ለራሱ አይታየውምና የፊቱ ክብር ለሙሴ አልታወቀውም፡፡
ይህ የሙሴ የፊቱ ማንጸባረቅ በብዙ ቅዱሳን ታሪክ ላይ የምናነበውና እግዚአብሔር ለሚወዳቸው የሚሠጠው አንዱ ክብር ነው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት ከመቀበሉ አስቀድሞ በሸንጎ ውስጥ እያለ ‹ፊቱ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ› ሰዎች ተመልክተው የነበረው ሙሴ ላይ ያበራው የእግዚአብሔር ክብር በእርሱ ላይ ስላረፈ ነበር፡፡ (ሐዋ. ፮÷፲፮)

በብዙ ቅዱሳን ገድላትም ላይ ፊታቸው ሲያበራ ሰዎች ያዩአቸው ቅዱሳን ታሪክ እናገኛለን፡፡ እንዲያውም አንድ ትሑት አባት የፊታቸው ብርሃን ለሌሎች ታይቶ ለከንቱ ውዳሴ ፈተና እንዳያጋልጣቸው ብለው ሰው እንዳያገኛቸው በጨለማ ይወጡ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ክብር አለመፈለጋቸውን አይቶ በጨለማ ፊታቸውን አብርቶ ሰው ሁሉ የነጋ መስሎት ከቤቱ እንዲወጣና ክብራቸውን እንዲያውቅ አድርጎባቸዋል፡፡ ይህ ክብር ለሁሉም ጻድቃን በሰማይ ይሠጣል፡፡ ‹‹በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ›› (ማቴ. 13፡42) ይህ ብርሃን እግዚአብሔር ለመንግሥቱ ቢያበቃን ለእኛም የተዘጋጀ ክብር ነው፡፡ ‹‹እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።›› (2ቆሮ. 3፡18)

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ፊቱ ሲያበራ ታዲያ ለማየት እስኪሳናቸው ድረስ ስላበራባቸው አሮንና የእስራኤል ልጆች ሙሴን ‹ተሸፈንልን› (ተገልበብ ለነ) ሊሉት ተገደዱ፡፡ ለጊዜው ታይቶ የተሻረውን የሙሴን የፊቱን ክብር (ብርሃን) ማየት ስላልቻሉ በጽላቱ ላይ የተጻፉትን ዐሠርቱን ትዕዛዛት ለማንበብ ሲቆም ሙሴ ሕዝቡን እንዳይቸገሩ ብሎ ፊቱን በመጋረጃ ይሸፍን ነበር፡፡ ወደ ምስክሩ ድንኳን ሲገባ መሸፈኛውን ይገልጥና ወደ እነርሱ ሲመለስ ግን ይሸፍነው ነበር፡፡ (ሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ "ሙሴ ፊቱ ሲያበራ በልብሱ ሸፍኖት ነበር ፣ የሙሴ አምላክ ክርስቶስ ግን በታቦር ተራራ ፊቱ ሲያበራ በልብሱ እንዳይሸፍነው ልብሱም ያበራ ነበር" ብለው ተቀኝተዋል።)

ቅዱስ ጳውሎስ ሙሴ ትእዛዛቱን ሲያነብ የተሸፈነበትን ያንን መጋረጃ የሙሴን ፊት ብቻ ሳይሆን ብሉይ ኪዳንም ሳይቀር ለእስራኤል የተሸፈነባቸው ለመሆናቸው ማሳያ አድርጎ አቅርቦታል፡፡

‹‹ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል።›› በማለት ኃጢአትን ቆጥራ ታስፈርድ በነበረችው በኩነኔ አገልግሎት (በኦሪት ፈንታ) የተተካችው አዲሲቱ የጽድቅ አገልግሎት (ወንጌል) ያልተከደነች እንደሆነችና የብሉይ ኪዳንን ምሥጢራት ሁሉ የምንረዳው ያለማወቅ መጋረጃን ወዳነሣልን ወደ ክርስቶስ ዘወር ብለን ስንመለከት መሆኑን አስረድቶናል፡፡ (2ቆሮ.3፡7-16)

የሙሴ ፊቱ ያበራው ለምን ነበር?

እስቲ ወደ ሙሴ እንመለስና እንጠይቅ! እስራኤል ለምን መሪያቸውን ትኩር ብለው መመልከት ተሳናቸው? ካህኑ አሮን እንዴት ወንድሙን መመልከት አስቸገረው? የሕዝቡ አለቆች እንደወትሮው ከሙሴ ላይ ማተኮር ለምን ተቸገሩ? ያለ ወትሮው የሙሴ ፊት ለምን አንጸባረቀ? ብለን ስንጠይቅ ሙሴ ያለማቋረጥ በደመና መካከል ከእግዚአብሔር ጋር ስለቆመና ቃል በቃል ለአርባ ቀንና ሌሊት ከአምላኩ ጋር ስለተነጋገረ ነበር፡፡ ስለተቀበለው የኦሪት ሕግ ክብር ሲባል የሙሴ ፊት በክብር አንጸባረቀ፡፡ የእግዚአብሔር ክብር በዙሪያው ስለነበር ፊቱ አንጸባረቀ ፤ ትኩር ብለው ማየት ቢሳናቸውም ዕድለኞች የነበሩት የዚያን ዘመን ሰዎች የሙሴን የሚያበራ ፊቱን ተመለከቱ፡፡

እስቲ ከፈጣሪው ጋር የተነጋገረውን የሙሴን ፊት በዓይነ ሕሊናችን ሲያንጸባርቅ እንመልከተው! በዘመኑ ባንኖርም ለአፍታ ያን ትሑት ሰው ሙሴን ዐሥርቱ ትእዛዛትን በጉያዎቹ ታቅፎ ከሲና ተራራ ሲወርድ ፣ ፊቱም ሲያበራ እንመልከተው......! ዕፁብ ድንቅ ነው!

ውድ አንባቢያን! በሲና ተራራ በደመና ተሸፍኖ ፈጣሪውን ያነጋገረው ሙሴ ፊቱ እንዲህ ካበራ ‹እግዚአብሔር በብሩሕ ደመና ተጭኖ መጥቶ በማኅጸኗ ያደረ› የድንግል ማርያም ፊትዋስ እንዴት ያበራ ይሆን? ሙሴ በእሳት መጋረጃዎች መካከል አልፎ ዐሠርቱን ቃላት በመቀበሉ ፊቱ ካንጸባረቀ ሰባቱ የእሳት መጋረጃ በሆድዋ ውስጥ ተዘርግቶ ለእግዚአብሔር ቃል ማደሪያ የሆነች የእመብርሃን ፊትዋ እንደምን ያንጸባርቅ ይሆን?

ለእኔስ ሁለቱን ጽላት ከታቀፈው ከሙሴ ፊት ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል የታቀፈችው የእመቤታችን ፊት እንደሚያበራ ይታየኛል፡፡ ሙሴ ለአንድ ወር ከዐሥር ቀን ያነጋገረውን ፈጣሪ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅጸንዋ ይዛ የወለደችው ድንግል የፊትዋ ብርሃንዋ መጠን ምን ያህል ይሆን? ሊቃውንቱ ዛሬ ሌሊት ‹ትበርህ እምኮከበ ጽባሕ ወታስተርኢ እም አርእስተ አድባር› ከጠዋት ኮከብ ይልቅ ታበራለች ከተራሮችም ራስ በላይ ትታያለች ይላሉ፡፡ አክለውም ‹ፈጽማ ያማረች ፣ የጸዳች እና የምታበራ ፣ እንደ ፀሐይ የምታበራ ናት› (አዳም ወሠናይት ጽዱት ወብርህት ከመ ፀሐይ ብርህት) ሲሉ ያድራሉ፡፡ እንደ ፀሐይ ብቻ ነው ወይ የምታበራው የሚል ካለ ደግሞ ‹‹ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበሪ ክብርሽ ከአድባራቱ ሁሉ ከፍ ከፍ ያለ›› እያልንም እናመሰግናታለን፡፡

የሙሴን ፊት ትኩር ብሎ ማየት ካስቸገረ እመቤታችንን ያዩ ሰዎች ምንኛ በብርሃን ተሞልተው ይሆን? ‹አሕዛብ ለፊትሽ ይማልላሉ› እንዳለው የእግዚአብሔርን እናት ያዩ ዓይኖች ምንኛ ክቡራን ናቸው! እንደ አባ ይስሐቅ ‹አርእየኒ እምከ› ‹እናትህን አሳየኝ› ሳይሉ ፤ እንደ ዮሐንስና እንድርያስ ‹ማደሪያህ ወዴት ነው?› ብለው ሳይጠይቁ እመቤታችንን ያዩ ዓይኖች ምንኛ ዕድለኞች ናቸው፡፡

ሰዎች ጠፈርን አዩ ተብሎ ዝናቸው ይነገራል፡፡ ጠፈሩንም ምድሩንም በመሃል እጁ የያዘን ጌታ በእቅፍዋ የያዘችውን እመቤት ከማየት በላይ ምን ክብር አለ፡፡ ጌታ የተወለደበትን ሥፍራ ማየት ድንቅ ነው ፤ የወለደችውን ማየት ምንኛ ታላቅ ይሆን? የእናንተን አላውቅም ፤ እኔ ግን እንደ ቅዱስ ዳዊት የአምላክን ማደሪያ አይ ዘንድ እመኛለሁ፡፡ ‹መቅደሱንም እመለከት ዘንድ› (መዝ.27፡4) በሰው እጅ ከተሠራው መቅደስ ይልቅ ልዑል ራሱ የሠራትን ሕያዊት መቅደስ ድንግል ማርያምን ማየት ይበልጣል፡፡ ሰማይንና ምድርን ሙሉ ከማየት እርስዋን ማየት ይበልጣል ፤ ሰማይ ዙፋኑ ነው ፣ ምድርም የእግሩ መረገጫ ነው ፤ ድንግል ማርያም ግን እናቱ ናት፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ እንዳለው ሰማይ አላጠባውም አላቀፈውም አላሳደገውም እርስዋ ግን ይህንን ሁሉ አድርጋለች፡፡ አባ ጊዮርጊስ እንዲህ ይላል ‹‹የሽቱ ዕቃ ሽቱው ካለቀም በኋላ መዓዛው ከዕቃው አይለይም፡፡ እመቤታችን ጌታን ከወለደችም በኋላ የመለኮቱ መዓዛ አልተለያትም››

የጌታችንን የክብሩን መጠን የተረዳ ሰው ማደሪያው የሆነች እናቱን እመቤታችንን ይወድዳል፡፡ እንኳንስ የወለደችውን እናቱን ቀርቶ የለበሰውን ልብስ ሳይቀር አክብሮ ነክቶ ይፈወሳል ፣ ያደረገውን ጫማ እንኳን ልፈታ አይገባኝም ይላል፡፡

ይህን የእመቤታችንን ፍቅር ስንረዳ በሰማያት የጌታ ማደሪያ ወላዲተ አምላክ ወዳለችበት ፣ በደስታ ወደ ተሰበሰቡት አእላፍ መላእክት ማኅበር ገብተን ለማየት እንበቃለን። ከሁሉም በላይ ከተአምረ ኢየሱስ በፊት "ለላህይከ ንትሜነይ ከመ ንርአዮ" (ውበትህን ልናይ እንወዳለን) እያልን የምንለምነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማየትም እንደርሳለን።

መጽሐፉ "በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል" ይላል። በታናሽዋ ብርሃን በድንግል ማርያም ያልታመነ ታላቁን ብርሃን ክርስቶስን እንዴት ሊያይ ይችላል? "ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ባለን" በመጥምቁ ዮሐንስ ብርሃንነት ካልታመንን ወደ "ብርሃናት አባት" እንዴት እንደርሳለን? (ዮሐ 5:35 ፣ ያዕ 1:17) ዳዊትስ "በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን" ብሎ የለ? (መዝ 36:9)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

አስተያየቶች