✞ ጥር 7 ሥሉስ ቅዱስ✞

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን ✞
✞ ጥር 7 ሥሉስ ቅዱስ✞
+ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር: በትሕትናም
ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም::
+እግዚአብሔር አንድም ነው: ሦስትም ነው:: ጊዜ
ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም:
በአካል: በግብር
ሦስትነቱ: በባሕርይ: በሕልውና: በመለኮትና በሥልጣን
አንድነቱ የጸና አምላክ ነው::
+ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ
ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው:: ዓለምን ከፈጠረ በኋላም
ምሥጢረ ሥላሴ
(መለኮት) ብለን የምንማረው ትምሕርት እንድንና
እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው::
+ይኼውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት
ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው:: ከዚህ አልፈን
በሥጋዊ አዕምሯችን
ጌታን 'እንመርምርሕ' ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት:
ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም::
+እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም
ፈጠረ:: እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ:- ስሙን
ቀድሰን
ክብሩን እንድንወርስ ነው:: ከዚህ የተረፈውን ምክንያት
ግን ራሱ ባለቤቱ ያውቃል::
+በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ
(አራትነት) የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ
ፈጣሪ
እግዚአብሔር ነው:: አብ: ወልድ: መንፈስ ቅዱስ በስም:
በአካል: በግብር ሦስትነት በባሕርይ: በሕልውናና በፈቃድ
አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ
ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ
ናቸውና::
+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ"
እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን)
አይጠሉም::
የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም
መጥተው ያድራሉ::
+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን
ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን
ቅዱስ
አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ
ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል::
+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89
ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም
እግራቸውን
አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ
አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት::
በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት::
+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኳን (ሐይመት) የድንግል
እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ አብ
ለአጽንኦ:
መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ: ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ
በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::
+በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ 2 ምክንያቶች
ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን 2ኛው
ደግሞ
ቅዳሴ ቤታቸው ነው::
+" ሕንጻ ሰናዖር "+
+ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ
እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም:
ለንጉሡም
በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በኋላ
ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::
+ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በኋላ በሥፍራው
በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን
ስማችን
የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን
በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::
+ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው
መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል::
ቀጥለውም ጦር
እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::
+መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ
ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም
እየተሠራ ያለው
ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ
ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::
+ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው:
ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል
ኪዳን
አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ
ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::
+ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቋንቋዎች
ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ::
ሥላሴም ያን ሕንጻ
በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ
ሥፍራው 'ባቢሎን (ዝሩት)' ሲባል ይኖራል::
+" ቅዳሴ ቤት "+
+ልክ የዛሬ 323 ዓመት: አድያም ሰገድ ኢያሱ
በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት: (ማለትም በ1684
ዓ/ም) በጐንደር
ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን
ተሰርታ ተጠናቃለች::
+ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ
ምዕመናን: ሠራዊት: መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት
ቅዳሴ ቤታቸው
ተከብሯል:: በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጓል:: ኢያሱ
አድያም ሰገድ ኃያል: ደግ: ጥበበኛ: አስተዋይ: መናኝ
ንጉሥ ነውና::
+ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር
ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች
በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ
ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ/ም በልጁ በአፄ
ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው፡፡
መልካም በዓል ይሁንልን አሜን!!!

አስተያየቶች